Tuesday, March 6, 2012

ለሙስሊም ወዳጆቻችን ጥያቄዎች የተሰጠ ምላሽ

ለሙስሊም ወዳጆቻችን ጥያቄዎች የተሰጠ ምላሽ



ሀንስ ሞሪን



ትርጉም
አዳነው ዲሮ





በደራሲው ፈቃድ የተተረጎመ

2003 ዓ.ም.


________________________________________________

CMM
2032 E Kearney, Suite 205
Springfield, MO 65803-4666
U.S.A.

የእንግሊዘኛውን ቅጂ ለማየት የሚሹ ከሆነ፣ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ። 

_______________________________________________
ጠቃሚ ምክሮች
በጽሑፎቹ መካከል በብራኬት [ ] የገቡ ማብራሪያዎች የተርጓሚው ተጨማሪ አሳቦች ሲሆኑ፣ ከቁርአን በተወሰዱት አንቀጾች (አያት) መካከል የሚታዩ ቅንፎች ( ) ግን በቀጥታ ከቁርአኑ የተወሰዱ ናቸው፡፡

ከቁርአን የተወሰዱ የእንግሊዘኛው አንቀጾች (አያት) ከአማርኛው ትርጉም ጋር አብረው እንዲቀርቡ የተደረገበት ምክንያት አማርኛው ትርጉም ውስጥ የሚስተዋሉ ብዥታዎችን ግልጽ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡

የተርጓሚው መግቢያ
እስልምና በ7ኛው ክፍለ ዘመን (እ.ኤ.አ. በ622 ዓ.ም.) በአንድ የአረብ ነጋዴ በመካ፣ ሳውዲ አረቢያ የተጀመረ ሐይማኖት ነው:: ይህ ሰው ሙሐመድ (እ.ኤ.አ. 570 ተወለደ) ይባላል:: ይህ እምነት በይበልጥ ተስፋፍቶ የሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ሲሆኑ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ የተከታዮቹ እንዳሉት ይነገራል፡፡ በተከታዮች ብዛት ከክርስትና ቀጥሎ በአለም ሁለተኛ ሃይማኖት ሲሆን በስሩ ሶስት ዋና ዋና የእምነት ልይኑቶች (denominations) አሉት፤ እነሱም፡- ሱኒ፣ ሺአት፣ እና ሱፊ ናቸው፡፡ የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ ቁርአን ሲሆን የእምነቱ ዋና ቋንቋም አረብኛ ነው፡፡ እንደ ሙስሊሞች እምነት ቁርአን እግዚአብሔር ለመጨረሻውና (ተተኪ ለሌለው) ነብይ (ሙሐመድ) የገለጠው መፅሐፍ ነው:: የእስልምና የእምነት አባቶች ሼክ፤ ኢማም (ሺአት) ሲባሉ የማምለኪያ ሥፍራው ደግሞ መስጂድ ይባላል፡፡

እስላም ማለት ‹‹ለፈጣሪ በመገዛት ውስጥ ያለ ሰላም›› ማለት ነው፡፡ ሲሆን ‹‹ማንኛውም ለፈጣሪ ፈቃድ ራሱን የሚያስገዛ ሰው ሁሉ ደግሞ ሙስሊም ይባላል፡፡

ሁሉም ሙስሊሞች አረቦች አይደሉም፡፡ እስልምና በተለያዩ ዘሮች ውስጥ ያለ ሃይማኖት ነው፡፡ ከአጠቃላይ የእስልምና ሃይማኖት ቁጥር አንጻር አረቦች 20% ብቻ ይይዛሉ፡፡ ከፍተኛ የእስልምና ተከታይ ቁጥር ያለባት አገር ኢንዶኔዢያ ስትሆን በዚህች አገር ያሉ የእስልምና ተከታዮቹም 120 ሚሊዮን ይደርሳሉ፡፡

አንድ ሰው ሙስሊም ለመሆን የሚጠበቅበት አንድና ዋነኛ ነገር ሻሃዳህን መፈጸም ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ፈጣሪ ብቻ እንዳለ እና ሙሐመድ ደግሞ የሰው ልጆች የመጨረሻ ነቢይ መሆኑን በአንደበቱ መናገር ማለት ነው፡፡
  
ሙስሊሞች በቁርአን ውስጥ አላህ እራሱን በ99 የተለያዩ ስሞች ገልጧል ብለው ያምናሉ፡፡ የሰው ልጅ ስለ ፈጣሪ ማንነት ሊያውቅ የሚችለውም በእነዚህ ስሞች አማካኝነት ነው ይላሉም፡፡ ከእነዚህ ስሞች ዝርዝር ውስጥ ለአብነት፡- መኃሪ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ጠባቂ፣ ሰጪ፣ የቅርብ አምላክ፣ የመጀመሪያው፣ የመጨረሻው፣ የተሰወረ፣ እና የሰላም ምንጭ የሚሉት ይገኛሉ፡፡
  
ሙስሊሞች በቀደሙት ነቢያት (በአስተምህሮአቸው መሠረት ይህ ነቢይነት የሚጀምረው ከአዳም ሲሆን የሚጨርሰው ደግሞ ሙሐመድ ላይ ነው) ማለትም ከአዳም እስከ ኢየሱስ ድረስ ባሉት ያምናሉ፡፡ ሙስሊሞች እነዚህ ነቢያት ሳይቀሩ ለፈጣሪ ፈቃድ ራሳቸውን አዝገዝተዋልና ሙስሊሞች ናቸው ብለውም ይመሰክራሉ፡፡

የእስልምና ቅዱሳት መጻሕፍት (ቁርአን እና ሱናህ)
የሲራ (Sira) እና የሐዲት (Hadith) ቅዱሳት መጻሕፍት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ከቁርአን በመቀጠል ልዩ ሥፍራ ያላቸው የእስልምና ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው፡፡ እስልምና በቁርአን፣ በሲራ (የሙሐመድ ባዮግራፊ/የሕይወት ታሪክ)፣ እና በሐዲት (የሙሐመድ ትራዲሽኖች/ልማዶች) ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ማለትም ሲራ እና ሐዲት የነቢዩ ሱናህ (Sunnah) በመባል ይታወቃሉ (ሱናህ የሙሐመድ ቃሎችና ተግባራት ማለት ነው)፡፡

ሱናህ Sunnah (سنة [ˈsunna], በብዙ ቁጥር سنن sunan [ˈsunan] የአረብኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ልማድ/ልምድ ወይም ተዘውትሮ የሚደረግ ድርጊትን ያመለክታል፡፡ ይህ ቃል ከእስልምና ሃይማኖት አጠቃቀም አንጻር ሲታይ ደግሞ የእስልምና ነቢይ የሆነውን የሙሐመድን አባባሎች/ንግግሮች፣ ፈለጎች እና የአኗኗር ልምዶች ያመለክታል፡፡

ቁርአን ‹‹ሙሐመድ ከአላህ ዘንድ የተቀበለው የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ›› ቢሆንም ብቻውን ስለ እስልምና የተሟል መረጃና መመሪያ አይሰጥም፡፡ ቁርአን በውስጡ በተደጋጋሚ የሰው ልጆች በሞላ የሙሐመድን ፈለግ (ቃሎችና ተግባራት) እንዲከተሉ ቢያዝም (ለአብነት 3:32) እነዚህን የሰው ልጅ እንዲከተላቸው የታዘዘውን የሙሐመድን ፈለጎች በስፋት ማግኘት የሚቻለው በቁርአን ውስጥ ሳይሆን በሲራ እና በሐዲት ውስጥ ነው፡፡

የሙሐመድ ሱናህ - የሙሐመድን የራሱን ቃሎች፣ ልምዶች፣ የዘወትር ተግባራት፣ የጥሞና ይሁንታዎቹን (silent approvals) ከማካተታቸው በተጨማሪ እንዴት ከወዳጆች ጋር፣ ከቤተሰብ ጋር፣ እና ከመንግስት ጋር መስተጋብር መፍጠር እንደሚቻል ምልከታን የሚሰጥ ስለሆነ በእስልምና ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡

እንግዲህ ከላይ አንደተገለጸው፣ እነዚህ የሙሐመድ ሱናዎች (የሙሐመድ ቃሎችና ተግባራት) በጽሑፍ መልክ ሰፍረው የሚገኙት በሁለት የተለያዩ የሙስሊም ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ አንደኛው ሲራ ሲባል ሁለተኛው ደግሞ ሐዲት ይባላል፡፡ (ሲራ + ሐዲት = ሱና)፤ (ቁርአን + ሱና = እስልምና)፤ በሚል የሂሳብ ስሌት በእስልምና ቅዱሳት መጽሐፍት መካከል ያለውን ግንኙነት መናገር ይቻላል፡፡

እስላማዊው ሊቅ ሃቢብ ኡር ራህማን አዛሚ ቁርአን በሐዲትና በሲራ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ እና ሸሪያም እንኳን ሙሉ የሚሆነው ከቁርአን እና ከሱናህ ጋር ከተረዳዳ ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ የእስልምና አስፈላጊ ልምምዶች እና እምነቶች የተቀዱት ከሱናህ ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ሱናህ ለእስልምና በጣም ጠቃሚ የመንፈሳዊ እውቀት ምንጭ ቢሆንም ምንጩ ቁርአን ሳይሆን ሐዲት እና ሲራ መሆናቸውን አንባቢ ልብ ይሉዋል፡፡ 

ስለ እነዚህ እስላማዊ ፅሑፎች ተአማኒነትና ህጋዊነት በተመለከተ የሙስሊም ምሁራን በቁርአን መግቢያ ሐዲትን አስመልክተው የፃፉትን እስቲ አብረን እንመልከት:- ‹‹ቁርአን እስልምናን ካቆሙ ሁለት እግሮች አንዱ ነው:: ሁለተኛው እግር የነብዩ ሱናህ ነው:: ቁርአንን ከሱናህ የሚለየው አፃፃፉ ነው:: ቁርአን በቀጥታ የወረደ የአላህ ቃል ሲሆን' የሐዲት ጥንቅር የሆነው ሱናህ ደግሞ በአላህ መንፈስ መነዳት (inspiration) የተፃፈ የነቢዩን ቃሎችና ድርጊቶች የሚተርክ ነው:: ቁርአን በሰዎች ቃላት አልተገለፀም:: ቃሎቹ' ፊደል-በፊደል ከአላህ የተሰጡ (የተወረዱ/የወረዱ) ናቸው:: ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ልጆች ከአላህ የተላከ የመጨረሻ መልዕክተኛ ነው:: ስለዚህ ቁርአን አላህ ለኛ የላከው የመጨረሻ መልዕክት ነው:: ከእርሱ በፊት የነበሩት እነ ኦሪት፣ መዝሙረ ዳዊትና ወንጌል ሁሉ በእርሱ ተውጠዋል::››

የኢሻቅ (Ishaq) ግለ ታሪክና የታባሪ (Tabari) ታሪክ በሐዲት ውስጥ ይታቀፋሉ፤ ሱናህዎች በመሆናቸው እስላማዊ ጥቅሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሱናህዎች ብቻቸውን የእስልምና ሃይማኖትን አፅመታሪክ፣ አውድና የታሪክ ቅደም ተከተል ይሰጡናል፡፡ ቁርአን እነዚህ ሱናህዎች በሚሰጡን ጊዜዎችና ቦታዎች ላይ ካልተደገፈ በቀር ግልጽ አይሆንም፡፡ የተቀረውም ሐዲት ቢሆን ዋጋው ዝቅ ይላል፡፡ ያለ ወንጌል ክርስትናን እንደማሰብ ማለት ነው፡፡ የታባሪ ተረጓሚዎች እንዲህ ይላሉ፣' "ሙሐመድ ኢብን ኢሻቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የነብዩን ግለ-ታሪክ የዘገበ ታዋቂ ሰው ነበር:: የእርሱ ሲራ የሙሐመድን የህይወት ዘመን ታሪኮች በተገቢው ደረጃ ያስቀመጡ ናቸው፡፡" 

በርካታ ሐዲቶች ሲኖሩ ዋነኛዎቹ በቡካሪ የተጠናቀሩቱ ናቸው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ማሱድ አል-ሐሰን ገለጣ ዋናዎቹ ስብስቦች፡-

የታወቁት (እውቅና) የተሰጣቸው የሐዲት ስብስቦች በ ‹ሙስናፍ› (1) ምሳሌ የሚከተሉት ስብስቦች ናቸው፡-

1. አል ቡካሪ (870 ሒጂራ) (የ7658 ሐዲቶች ስብስብ)
2. ሙስሊም (875 ሒጂራ) የ7748 ሐዲቶች ስብስብ)
3. አቡ ዳውድ (875 ሒጂራ) (የ5276 ሐዲቶች ስብስብ)
4. አል ቲርሚዚ (892 ሒጂራ) (የ4415 ሐዲቶች ስብስብ)
5. አል-ናሳይ (915 ሒጂራ) (የ5776 ሐዲቶች ስብስብ)
6. ኢብን ማጃ (886 ሒጂራ) (የ4485 ሐዲቶች ስብስብ)

የአል-ቡካሪና የአል-ሙስሊም ስብስቦች ከሌሎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስልጣን ያላቸው መሆናቸውን ለማሳየትም ‹አል-ሳሂሃይን› ተብለው ይጠራሉ፡፡   

ሲራ የእስልምና ሕግን (ሸሪያ) ለመመስረት እና ቁርአንን ለማብራራት/ለመተርጎም ልዩ ስፍራ አለው፡፡ በጣም ተቀባይነት ያለውና ስልጣን ያለው የሙሐመድ ሲራ በኢብን ኢሻቅ የተዋቀረው ነው፡፡ ሁለቱ ጥንታዊ ሲራዎች የሚከተሉት ናቸው፡- (1) መሐመድ ኢብን ኢሻቅ (773) በኢብን ሂሻም በኩል (840 ሒጂራ) የክለሳ ስራ፣ Sirat Rasul Allah. (English translation 798 pages[3].) እና (2) መሐመድ ኢብን ሳዓድ (852 ሒጂራ) Kitab al-Tabaqat al-Kabir, (English translation, 1097 pages [4].)

ስድስቱ የእስልምና ሃይማኖት መግለጫዎች
እነዚህ ትምህርቶች የእስልምና መሠረታዊ እምነቶች ናቸው፡፡ ማንኛውም ሙስሊም እውነተኛ ሙስሊም ለመባል እነዚህን መሠረታዊ የእምነት አቋማት ሊከተላቸውና ሊፈጽማቸው ይገባል፡- (1) በአንድ ፈጣሪ ማመን (2) በሁሉም የፈጣሪ ነቢያት ማመን (3) ከአላህ ዘንድ ለነቢዩ ሙሴ፣ ለዳዊት፣ ለኢየሱስ እና ለሙሐመድ በተገለጡትን ቀደምት የቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎች ማመን (4) በመላእክት ማመን (5) ስለ ፍርድ ቀን እና ከዛ በኋላ ስላለው ሕይወት ማመን (6) በመለኮታዊ አዋጅ (ወይም የፍጻሜ እጣ ፈንታ) ማመን፡፡

አምስቱ የእስልምና አዕማዳት
(1) እምነትን መመስከር (ሻሃዳህ) ፈጣሪ አንድ መሆኑን እና ሙሐመድ የመጨረሻው የሰው ልጅ ነቢይ ነው ብሎ መናገር፡፡ (2) የየዕለት ጸሎት (ሶላት) በቀን አምስት ግዜ መጸለይ፡- በአምስቱ የዕለት ተዕለት ጸሎት አንድ ሙስሊም ፊቱን መካ ወደሚገኘው ካአባ አዙሮ መጸለይ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ባለ ስድስት ጎን ቅርጽ ያለው ድንጋይ (ካአባ) በሙስሊሞች ዘንድ መጀመሪያ በአዳም የተገነባ እና በመቀጠልም በአብርሃም የታደሰ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሙስሊሞች ካአባ ለአንዱ አላህ በምድር ላይ የተሰራ የመጀመሪያ የማምለኪያ ሥፍራ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ሃጅ፣ ወደዚህ ሥፍራ በየአመቱ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ (3) ምጽዋት/ቀረጥ (ዘካ) በየአመቱ መጨረሻ ለችግረኞች የሚሰጥ ስጦታ፡፡ አንድ ሰው ከቆጠበው ሃብት ላይ 2.5 እጁን ለተቸገሩ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡ (4) የሃይማኖት ጉዞ (ሀጅ) አካላዊ እና የገንዘብ ችግር ከሌለ በስተቀር ቢያንስ አንድ ግዜ ወደ መካ መሄድ፡፡ (5) የሮሞዳን ጾም (ሳውም)፡፡

የቁርአን ይዘት
ብዙዎቹን የተውራት/ኦሪት (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) እና የታልሙድ [1] ታሪኮች በቁርአን ውስጥም ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ ምንም እንኳ በቁርአን ውስጥ ሰፍረው የምናገኛቸው በርካታዎቹ ገጸ-ባሕሪያት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታልሙዱ ጋር ተመሳሳይ ቢሆኑም የታሪኮቹ አውድ እና መቼት (ጊዜ እና ቦታ) ግን ልዩነት አላቸው፡፡ በቁርአን ውስጥ ቁርአን የጠቀሳቸውና በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ ገፀ-ባህሪያት 4 ብቻ ናቸው:: ከእነዚህም ሁለቱ በአፈታሪክ አገር የኖሩ አፈታሪክ ሰዎች ሲሆኑ 3ተኛው ደግሞ የሙሐመድ ትልቁ ነቃፊ (ተቺ) የነበረው አጎቱ አቡ ለሀብ ነው:: አራተኛው ደግሞ በአላህ መሰረት የእስላሞች ነብይ የነበረው ታላቁ እስክንድር ነው::

የተቀሩት ገፀ-ባህሪያት ማለትም፡- አዳም (አደም)፣ ኖህ (ኑሕ)፣ አብርሃም (ኢብራሂም)፣ ይስሀቅ (ኢስሓቅ)፣ እስማኤል፣ ያዕቆብ፣ ኢያሱ (አልየሰዕ)፣ ሎጥ፣ ሙሴ (ሙሳ)፣ አሮን (ሃሩን)፣ ዮናስ፣ ዳዊት (ዳውድ)፣ ሰለሞን (ሱለይማን)፣ ማርያም (መርየም)፣ ኢየሱስ (ዒሳ)፣ ሰይጣን፣ ገብርኤል (ጅብሪል) እና የመሳሰሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ታሪክ በቁርአኑ ላይ የሰፈረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው መሠረት አይደለም:: በቁርአን ውስጥ፣ በነዚህ ሰዎች ሕይወት ዙሪያ የቀረቡት ታሪኮች ወቅታቸውና አውዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱሱ ወቅትና አውድ ጋር አይጣጣምም፡፡

ሰው በእስልምና
ሰው የተፈጠረው በጭንቀት ውስጥ እንዲሆን ነው 90፡4፡፡ ሰው በመጀመሪያ የተፈጠረው ከሸክላ ነበር፡፡ እሱም ከዚያ የተፈጠረው እንደ ሸክላ ነገር ሆኖ ነበር ከዚያም ሕይወት ያለው ነገር (ጀርም) ሆኖ በማህፀን ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ጀርሙም ወደ ረጋ ደምነት ተቀየረ፡፡ የረጋውም ደም ወደ ትንሽ ስጋነት ሆነና ወደ አጥንትነት ተቀየረ፡፡ አጥንቱም ከዚያ በስጋ ተሸፈነ፡፡ ይህ አስደናቂ የዕድገት ሂደት ነው በዚህም ነው ሕይወት የሚፈጠረው እንደገናም የሚፈጠረው 23፡12-14፡፡ እያንዳንዱ ሰው የጀመረው እንደ ሚፈስ የወንድ ፈሳሽ ሆኖ ነው ይህም ወደ ረጋ ደምነት ተቀይሮ የወንድና የሴት አካል ክፍልነት ይለወጣል 76፡37-39፡፡

አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት በሰማይ ባለው የገነት አትክልት ቦታ ነው፡፡ ከሰይጣን በቀር መላእክት ሁሉ ለአዳም በመስገድ አላህን ታዘዋል፡፡ ሰይጣን ባለመታዘዙ የተነሳ ለዘላለም ተሽሯል፡፡ ሰይጣንም በበኩሉ አላህ እንዳይቀርቧት ካዘዘው ዛፍ እንዲበሉ አዳምንና ሔዋንን ፈተናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከሰማያዊቷ የአትክልት ቦታ አዳምንና ሔዋንን አላህ አስወጣቸው እና በምድር ላይ አስቀመጣቸው 7፡11-25፡፡

ልዩ የሆነው ሰው፡- ሁሉን ነገርን ለማድረግ የሚችል ታላቅ ሰው ተፈጥሮ ነበር፡፡ ስሙም ዙልቀርነይን የተባለ ነው፡፡ እሱም ወደ ሩቅ ምዕራብ ተጉዞ ፀሐይ ጥቁር ጭቃ ውስጥ ስትጠልቅ አያት፡፡ እዚያም ባሉ ሰዎች ላይ እንዲገዛ ስልጣን ተሰጠው በኃይልም ገዛቸው፡፡ ደግሞም እንደገና በሌላ መንገድ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ተጓዘ እዚያም ለፀሐይ መውጪያ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች አየ፡፡ እነሱም በጣም ከሚያቃጥለው የቀረበ የፀሐይ ብርሃን ኃይል መቃጠል የሚጠብቃቸው ማንም አልነበረም፡፡ እነዚያንም ሰዎች ብቻቸውን ተዋቸው፡፡ ሌላው እሱ ያደረገው ነገር ከብረት ቁራጮች ትልቅን ግድብ መስራትና በቀለጠ ነሐስም መሸፈን ነበር፡፡ እሱም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በሁለት ተራራዎች መካከል ያለውን ክፍት ቦታ ሞልቶት ነበር፡፡ ይህም የጎግ ማጎግ የተባሉት ሕዝቦች እንዳይደርሱበትና ጎረቤቶቻቸውን እንዳይረብሹ ነው፡፡ ይህም ታላቅ ግድብ እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ ይኖራል 18፡83-100፡፡

ሰይጣን በእስልምና
ከሰዎች መፈጠር አስቀድሞ ሰይጣን ጭስ ከሌለው እሳት ውስጥ ተፈጠረ፡፡ እሱም ከሸክላ ተገንብቶ ሕይወት እንዲኖረው ለተደረገው ለአዳም እንዲሰግድ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወሙ ተፈረደበት፡፡ እሱም ሲጠፋና ወደ ምድር ሲዋረድ ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት መሐላን ማለ፡፡ አዳምና ሔዋንም የእሱ የመጀመሪያ የጥፋቱ ተጎጂዎች ሆኑ፡፡ እሱም ከጂኒዎች አንዱ ነበረ 15፡28-39፣ 7፡11-23፣ 18፡50፡፡ ክፉ መናፍስት፡- ጂኒዎች የተሰሩት ጭስ ከሌለው እሳት ነበር 55፡15፡፡

ቁርአን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ፍርድበ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል፡- ፍርድን አስመልክቶ የተጻፉት ጽሑፎች በቀደሙት ቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ ማለትም በአብርሃምና በሙሴ መጽሐፍት ውስጥ ይገኛሉ 87፡17-19፡፡ የማያምኑት ሰዎች በሙሴና በአብርሃም መጽሐፍት ውስጥ የተሰበኩትን ስብከቶች በፍፁም አልሰሙአቸውምን? 53፡36-37፡፡ በአንድ አምላክ ማመን በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትምህርት የተሰጠበት እውነት ነው፡፡ የማያምኑቱ ለሙስሊሞች አንዳች ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ተጠይቀዋል 21፡24፡፡

ተጠራጣሪዎች ወደ አይሁዶችና ወደ ክርስትያኖች ተመርተዋል፡- አንተ መሐመድ የቁርአንን እውነተኝነት የምትጠራጠር ከሆነ ከአንተ ሕይወት በፊት የተገለጠውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡትን እነዚያን መጠየቅ ይኖርብሃል 10፡94፡፡ ሐዋርያትና ነቢያት በሙሉ ከመሐመድ በፊት መጥተው የነበሩት እሱ ተራ ሰው እንደሆነ እነሱም ተራ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህንን በተመለከተ ጥርጥር ያለ ከሆነ ሰዎች የመጽሐፉን ሰዎች (ክርስቲያኖችንና አይሁዶችን) መጠየቅ ይኖርባቸዋል 21፡7 16፡43፡፡ ለሰዎች ሁሉ መሪና በረከት ሆኖ ያስተምራቸው ዘንድ ለሙሴ ቅዱስ መጽሐፍ ተሰጥቶት ነበር 28.43 46.12፡፡

የአይሁድ ሕዝብ እና ቅዱሳን መጻሕፍት፡- የአይሁድ ሕዝብ ሕጉ ወይንም ቶራ (አምስቱ የሙሴ መጽሐፍትተሰጥቷቸው ነበር፤ ነገር ግን ለእሱ አልታዘዙም፡፡ እነሱም ልክ እንደ አህያ በከባድ መጽሐፍት ሸክም የከበደባቸው ነበሩ፡፡ እነሱ የተጠሉ ናቸው ምክንያቱም የአላህን መገለጥ አንፈልግም ብለዋልና፡፡ አይሁዶች የአላህ እውነተኛ ብቸኛ ጓደኞች ቢሆኑ ሊሞቱ ይመኙ ነበር፤ ነገር ግን አልተመኙም ምክንያቱም ስህተት የሆነውን ነገር ነውና ያደረጉት 62፡5-7፡፡ የእስራኤል ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን፣ ነቢይነትን ተሰጥቷቸው ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ ተመርጠው ነበር፡፡ መጽሐፉ ለእነሱ ከተሰጠ በኋላ ግን እርስ በእርሳቸው ተከፋፈሉ 45፡16-17፡፡ ለእስራኤልና ለሙሴ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲወርሱ ምሪት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህም ለሰዎች መረዳትን እንዲያገኙ መመሪያ ነው 40፡53-54፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን ታዟል፡- እነዚያ ለሐዋርያት የተሰጡትን ቅዱሳት መጽሐፍትን የማይቀበሉት በፍርድ ቀን በአንገቶቻቸው ላይ ሰንሰለት ተደርጎባቸው በፈላ ውሃ ውስጥ እየተጎተቱ ወደ እሳት የሚወረወሩት ናቸው 40፡69-72፡፡ በአላህ ፈቃድ ብቻ ተዓምራትን ያደርጉ የነበሩ ከመሐመድ በፊት የተላኩ ሐዋርያት ነበሩ፡፡ የእነሱም የአንዳንዶቹ ታሪክ በቁርአን ተተርቷል፤ የአንዳንዶቹም አልተነገረም 40፡78፡፡ እውነተኛ አማኞች በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት ናቸው 2፡4፡፡ ሙስሊሞች በአላህ በቁርአን እንዲሁም ለአብርሃም፣ ለእስማኤል፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ እና ለያዕቆብ ዘር ለሙሴ፣ ለኢየሱስ እና ለሌሎች ነቢያት ለተገለፀው እንደሚያምኑ መናገር አለባቸው 21፡36፡፡

አንድ ዓይነት እግዚአብሔር፡- ለመጽሐፉ ሰዎች ንገራቸው፤ እናንተ ሙስሊሞች ለእነሱ በተሰጠው በቅዱሳት መጽሐፍት እና በቁርአን እንደምታምኑ ንገራቸው፡፡ የእነሱ እግዚአብሔርና የምታምኑት እናንተ አላህ አንድ ዓይነት እንደሆነ ንገራቸው 29፡46፡፡

ቶራህ (አምስቱ የሙሴ ቅዱሳት መጻሕፍት) ታማኝ መጽሐፍ ነው፡- ቶራህ የአላህን ፍርድ የሚናገር መጽሐፍ ነው፡፡ እሱም የመገለጥ መሪና ብርሃን ነው 5፡4344፡፡
ወንጌል ታማኝ ነው፡- ኢየሱስ የማርያም ልጅ የመጣው ቀድሞ የተገለጠውን ቶራህን በማረጋገጥ ነው፡፡ እሱም ምሪትና ብርሃን ያላትን ወንጌልን ተሰጥቶት ነበር፡፡ እሱም ከቶራ ጋር የሚስማማ ነው፡፡ እናም ወደ ክፉ ለሚያዘነብሉት መሪና ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ክርስትያኖች ስለዚህም ሊፈረድባቸው የሚገባው በወንጌል ውስጥ አላህ በገለጠው መገለጥ መስረት ነው 5.4647፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ነው፡- ነቢያቱ ተመርጠው ተመርተው ነበር፡፡ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ እና ነቢይነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በመሐመድ ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አንቀበልም ቢሉ ቅዱስ መጽሐፍን ለሚያምኑ ለሌሎች ተላልፎ ይሰጣል 6.87-89፡፡

እግዚአብሔርን በግል ስለማወቅ፡- አንድ እግዚአብሔር ብቻ አለ፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች የራሳቸውን ልጃቸውን እንደሚያውቁ አድርገው ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ሌሎች በጣዖት አምልኮ መሠረት ነፍሳቸውን አጥተዋል ስለአላህም ውሸትን በመፍጠር እና ኃጢአታዊ ባህሪና መገለጥን በመካድ 6.20-22::

ለክርስትያኖችና ለአይሁዶች ተስፋ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እምነት ቢኖራቸውና ከክፉም ቢጠበቁ ይቅር ይባሉ ነበር፡፡ በቶራህና በወንጌል ላይ የተገለጠውን ቢጠብቁ ኖሮ ይሸለሙ ነበር 5.6566፡፡ እነሱም በቶራና በወንጌል ላይ የተጻፈውን የማይከተሉ ከሆነ ምሪትን አያገኙም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቅዱስ ቃላት የመለኮት መገለጦች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነሱን ማንበብ ዓመፀኝነትን አምጥቷል ይህም በእምነት ባልሆኑት ላይ ነው 5.68፡፡

እስላማዊ ምልክቶች
የሩብ ጨረቃ ቅርጽ እና ኮከብ

ዋና ዋና በአላት
ሮመዳን- አንድ ወር የሚቆይ
ኢድ አል-ፈጥር -የጾፍ መፍቻ
ሂጅራ- አንድ ሣምንት የሚቆይ
ኢድ አል-አድሃ - የመሥዋእት በአል

አስራ ሁለቱ ኢማሞች
1.      አሊ
2.     አል-ሃሰን
3.     አል-ሁሴን
4.     አሊ ዛይን አል-አብዲን
5.     ሙሐመድ አል-ባቂር
6.     ጃፋር አል-ሳዲቅ
7.     ሙሳ አል-ካዚም
8.     አሊ አል-ሪዳ
9.     ሙሐመድ አል-ታቂ
10.   አሊ አል-ናቂ
11.     አል-ሀሰን አል-አስካሪ
12.    ሙሐመድ አል-ማህዲ

ሲኦል በቁርአን  

ቁርአን ስለ ሲኦል ዘጠና አምስት ጊዜ ያህል የተናገረ ሲሆን ስለ ሲዖል የሚከተሉትን ጥቅሶች ይናገራል፡-

ሲዖልን መሙላት፡- አላህ ቢፈቅድ ኖሮ ለእያንዳንዱ ሰው እውነተኛ ምሪትን በሰጠ ነበር፣ ነገር ግን የአላህ ቃል የሚለው እሱ ሲዖልን በሰዎችና በጅኒዎች እንደሚሞላው ነው (32.13፣ 11.119፣ 7.18)፡፡

እሳት፡- ኃጢአተኛው በሲዖል ውስጥ ይቃጠላል 82.14፡፡ እሳቱም የሚለኮሰው በአላህ ነው እሱም እስከ ደረት ድረስ ከፍታ ያለው ነው በበላያቸው ተለኩሶ በዙሪያቸው ይከባቸዋል 104.6-9፡፡ በፍርድ ቀን ሰዎች በሲዖል እሳት ውስጥ ይላጫሉ ይህም እነሱ የካዱት እሳት ይህ ነው እየተባሉ እየተነገራቸው ነው እናም በስራቸው ውጤት የተነሳ እዚያ ውስጥ ይቃጠላሉ 52.11-16፡፡

መጠጥ፡- የማያምኑት በፍርድ ቀን የፈላን ውሃ እንዲጠጡ ይሰጣቸዋል 88.5፡፡

ምግብ፡- ሲዖል ውስጥ የሚኖረው ምግብ ዳሪዕ ብቻ ነው (እሾኸማ መራራ አትክልት ሲሆን ሽታውም መልኩም መጥፎ ነው)፡፡ እሱም ረሃባቸውን በፍፁም አያረካላቸውም 88.6፡፡ እዚያም የሚኖረው ብቸኛ ምግብ ከቁስል እጣቢ የሚመጣ ቆሻሻ ብቻ ነው 69.36፡፡ የነሱም ምግብ የሚሆነው ከዘቁም ዛፍ ነው ይህም የሚበለቅለው በሲዖል ጫፍ ላይ ነው ፍሬውም የሰይጣን እራስ የመሰለ ሲሆን እንዲጠግቡም ይበሉታል ከዚያም የፈላ ውሃን ጠጥተው ተመልሰው ወደሲዖል ውስጥ ይጣላሉ 37.62-68፡፡

ሰንሰለቶች፡- ሰዎች በሰንሰለት ታስረው ሰባ ክንድ እንዲጓዙ ይደረጋል 69.32፡፡ ከማንኛውም ለሐዋርያት በተሰጡት ቅዱስ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ ወይንም ቁርአን) ጋር የማይስማሙት እነዚያ በአንገቶቻቸው ላይ ሰንሰለት ታስሮባቸው በፈላ ውሃ ውስጥ ይጎተታሉ ከዚያም በፍርድ ቀን ወደ እሳት ውስጥ ይጣላሉ 40.69-72፡፡ እነሱም አብረው ታስረው በጠባብ ስፍራ ተጥለው ሞትን ይለምናሉ 25.13፡፡

የሹፈት ጥያቄዎች፡- ኃጢአተኞች በገነት ውስጥ በሚኖሩት ሰዎች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠየቃሉ፡- ‹ወደ ሲዖል እንድትጣሉ የተደረጋችሁት ምን ስለሰራችሁ ነው?› መልሳቸውም የሚሆነው እንዳልፀለዩና ረሃብተኞችን እንዳልመገቡ ነው፣ እንዲሁም ሰዎችን እንዳሙና የፍርድ ቀንን እንደካዱ ነው 74.40-46፡፡ የገነትም ነዋሪዎች በሲዖል ውስጥ ባሉት ላይ ያሾፉባቸዋል 7.44-50፡፡

ማለቂያ የሌለው ነው፡- በሲዖል ያለው ስቃይ በፍፁም አያቆምም እንዲሁም ደግሞ በሲዖል ያሉት እነዚያ ምንም ምህረት አይደረግላቸውም 16.85፡፡

በመላእክት ይማታሉ፡- የማያምን ሰው በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱን መላእክት ይሸከሙና ይወስዱታል ከዚያም ፊቱን እና ጀርባውን እየመቱት ‹የሲዖልን እሳት ስቃይ ቅመስ› ይሉታል 8.50፡፡
የብረት በትር፡- የማያምኑት በብረት በትር ይገረፋሉ (ይቀጣሉ) 22.21፡፡

መንግስተ ሰማይ በቁርአን
የሰው ስጋዊ ፍላጎቶች ይሟላሉ፡- ከሞት በኋላ ያለው የሙስሊሞች ሕይወት ፍላጎቶቻቸው ሁሉ የሚሟሉበት ቦታ ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ ነገር የሚሆንላቸው ቦታ ነው 50.35፡፡

ማለቂያ የሌለው የወይን ጠጅ ምንጭ፡- ፃድቃኖቹ ማለቂያ ከማይኖረው የወይን ጠጅ ምንጭ ይጠጣሉ ይህም ከካፉር ውሃ ጋር የተደባለቀ ነው (76.5-6)፡፡ እሱም ነጭ ወይን ነው የሚሆነው ነገር ግን በበረከት ገነት ውስጥ የሚኖሩትን አስካሪ አይሆንም 37.45-47፡፡

አትክልት ቦታዎች፡- ከሞት በኋላ የሚሆኑት ደስታዎች ከሁሉም ዓይነት ስጋዊ ደስታዎች በተሞሉት በሁለት የአትክልት ቦታዎች ውስጥ ነው የሚሆኑት 55.46-48፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ አትክልት ቦታዎች አሉ እነሱም ደስታዎችን የተሞሉ ናቸው 55.62፡፡

ደናግል፡- በአትክልት ቦታዎቹ ውስጥ ፍራፍሬዎች፣ ጥላ ቦታዎች፣ የውሃ ፏፏቴዎች እና ደናግል የሞሉባቸው ናቸው፡፡ ደናግሎቹም ደግሞ ዓይናፋርና እንደ (ያቁትና መርጃን ይመስላሉ እነዚህ ለጌጥ የሚሆኑ የሚያንፀባርቁ ክብር ድንጊያዎች ናቸው) 55.56፣ 58፡፡ እንዲሁም በሁለተኛው ገነት ውስጥ ደግሞ ጥቁር ዓይን ያላቸው ሰማያዊ አጃቢዎች ይኖራሉ እነሱም በትላልቅ ድንኳኖቻቸው ውስጥ እንዲቀመጡ ይገደዳሉ፡፡ ሰዎችም ሆኑ ጅኒዎች አልገሰሷቸውም፡፡ የነሱም ንፅህና ገነት መግባት የተሰጣቸው ገነት እስከሚደርሱ ድረስ የተጠበቀ ነው፡፡ እነሱም በአረንጓዴ አረግራጊ ምንጣፎችና ስጋጃዎች ላይ የተደላደሉ ሆነው ይጠባበቃሉ 55.76፡፡ እነዚያም የተጨጎሉት እኩያዎች እና ጡተ ጉቻማዎች ናቸው 78.33፡፡ በገነት ውስጥ ሙስሊሞች ከተጨጎሉት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነትን ያደርጋሉ እነሱም ትላልቅ ውብ የሆኑ ጥቁር ዓይኖች አሏቸው 52.20፤ 44.54፣ 2.25፡፡ ዓይናፋር የሆኑ ደናግሎች ይከቧቸዋል ልክ እንደ እንቁላል የሆኑ ትላልቅ የሚያምሩ ዓይኖች ያሏቸው ናቸው 37.48-49፡፡

ቆንጆ የሆኑ የወንድ ሰራተኞች፡- እነሱም የሚገለገሉት እንደ እንቁ ቆንጆ በሆኑ ወጣት ወንዶች ልጆች ነው፡፡ እነሱም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ይጠብቋቸዋል፡ 52.24፡፡
መብልና መጠጥ፡- በአትክልቱ ቦታ በከፍተኛው ላይ ሙስሊሞች እስከ ልባቸው ጥግ ድረስ ይበሉና ይጠጣሉ 69.24፡፡

ምስጋናና ሕብረት፡- በገነት ደስታ ውስጥ ወንዞች በነዋሪዎቹ እግር ድረስ ይፈሳሉ፡፡ እነሱም በደስታ ይጮኻሉ እርስ በእርስም ሰላምታን ይሰጣጣሉ እንዲህም ይላሉ ‹ሰላም› 10.9-10፡፡ እነሱም ቀንና ሌሊት ሳይታክቱ ውዳሴን ይሰጣሉ 41.38፡፡

ወርቅና ሐር፡- እነዚያ በዘላላም ገነት ውስጥ ያሉት በወርቅ የእጅ አምባርና በቀጭን አረንጓዴ ሐር ልብስ ያጌጣሉ እነዚህም በሐር ላይ በወርቅ በተጠለፉ ስራዎች ነው 18.31፣ 35.33፡፡

ምድራዊ ሚስቶችና ቤተሰቦች፡- የእስልምናን እምነት የሚከተሉ ልጆች ያሏቸው ሙስሊሞች በበረከት የገነት ቦታ ላይ ከልጆቻቸው ጋር ይገናኛሉ ይህም በምድር ላይ እያሉ የሰሩትን እንዳያጡ ነው 52.21፡፡ ሙስሊሞች በኤደን ገነት ውስጥ የሚገቡት እስልምናን እንደተከተሉት እንደ አባቶቻቸው፣ ሚስቶቻቸው እና ልጆቿቸው ነው 13.23፡፡

ትልልቅ የመኖሪያ ቤቶች፡- ይህ በአላህና በመሐመድ ማመን ያታዘዘ ነው፡፡ በሁሉም ነገር ስለ እስልምና መዋጋትና መጋደል የታዘዘ ነገር ነው፡፡ በሕይወትም እንኳን ቢሆን ስለዚህም ኃጢአቶቻቸው ይቅር ይባልላቸዋል እንዲሁም በገነት አትክልት ቦታ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል ትልልቅ የመኖሪያ ቤትም ይሰጣቸዋል 61.11-12፡፡ እንዲሁም እነዚያ የሚገባቸው፣ ወንዞች በስራቸው የሚፈሱላቸው ሰፋፊ ቤቶች ይሰጣቸዋል 39.20፡፡
  
ስለአይሁድና ክርስቲያኖች በቁርአን ውስጥ የተነገሩ አወንታዊ ንግግሮች
ለክርስትያኖችና ለአይሁዶች ሽልማት ይጠብቃቸዋል፡- ሙስሊሞች የሆኑት እነዚያ አይሁዶች ክርስትያኖችም እና ሳባውያን የሆኑት በአላህ ስላመኑ በመጨረሻው ቀን ሽልማት ይጠብቃቸዋል ስለዚህም መፍራትም ሆነ ማዘን የለባቸውም ስለዚህም መልካምን ይስሩ 2.62፡፡

ቀጥተኛ ደቀ መዛምርት፡- አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ቅዱሳት መጽሐፍትን ያስታውሳሉ ይህም በማታና በጠዋት ሲሆን ለአምልኮም ይሰግዳሉ፡፡ እነሱም በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነዋል ስለዚህም ፃድቃን ናቸው፡፡ እነሱም ይሸለማሉ፡፡ 3.113-115፡፡

እግዚአብሔርን በግል ስለማወቅ፡- አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ያለው፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁት ያህል ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ሌሎች በጣዖት አምልኮ አማካኝነት ነፍሶቻቸውን ስላጡ ስለ አላህም ሐሰትን ስለፈጠሩ በኃጢአት ባህርይ ስለሚኖሩና መገለጥንም ስለሚክዱ ነው 6.20-22፡፡

ተጠራጣሪዎች ወደ አይሁዶችና ወደ ክርስትያኖች ተመርተዋል፡- ‹አንተ መሐመድ የቁርአንን እውነተኝነት የምትጠራጠር ከሆነ እነዚያን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡትን መጠየቅ አለብህ ይህም ከአንተ በፊት የተገለጠውን ነው› 10.94፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በክርስትያኖችና በአይሁዶች ይጠና ነበር፡- ቅዱስ መጽሐፍን የወረሱት እነዚያ አጥንተዋቸዋል በሚገባም ያውቋቸዋል ስለዚህም ስለ አላህ ትክክል ያልሆነን ምንም ነገርን አያደርጉም 7.169፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች አንድ አይነትን መጽሐፍ ቅዱስን ስለማጥናታቸው ግን አይስማሙም 2.113፡፡

የኢየሱስ ተከታዮች ታዝኖላቸዋል፡- ኢየሱስ የማርያም ልጅ በሐዋርያትና በነቢያት ረጅም መስመር ተከትሏል፡፡ እሱም ወንጌል ተሰጥቶት ነበር አላህም በእሱ ተከታዮች ልብ ላይ ርህራሄንና ምህረትን አደረገ 57.27፡፡

አንድ አምላክ፡- ለመጽሐፉ ሰዎች ንገራቸው እናንተ ሙስሊሞች ለእነሱ በተሰጠው ቅዱስ መጽሐፍና ለእናነተ በተሰጠው በቁርአን እንደምታምኑ ንገራቸው፡፡ እንዲሁም የእነሱ እግዚአብሔርና የእናንተ አላህ አንድ አምላክ እንደሆነ ንገራቸው እንዲሁም እናንተ ለእሱ እራሳችሁን እንዳስገዛችሁ ንገራቸው 29.46፡፡

ለክርስትያኖችና ለአይሁዶች ስላለው ተስፋ፡- የመጽሐፉ ሰዎች የሚያምኑና ከክፉ የሚጠበቁ ከሆነ ይቅር ይባላሉ፡፡ በቶራና በወንጌልም ውስጥ ያሉትን የሚጠብቁ ከሆነ ይሸለማሉ 5.65፣66፡፡ በቶራና በወንጌል ውስጥ ያለውን ትምህርት ካልተከተሉ ግን ምሪትን ሊቀበሉ አይችሉም 5.68፡፡


ማውጫ


ሙስሊሞች የሚያነሷቸው የመከራከሪያ ነጥቦች


__________________________________________________________________________________________________________________________________


መግቢያ
ከክርስትና ውጪ፣ ሃይማኖቱን በሚሽን/በተልዕኮ በዓለም ላይ ለማስፋፋት ጥረት የሚያደርግ ብቸኛ ሃይማኖት እስልምና ነው፡፡ የእስልምና እምነት አስፋፊዎች የመጨረሻ ግብ ዓለምን በእስልምና መሸፈን መሆኑ ምስጢር አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሙስሊም፣ ሙስሊም ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን ወደ እምነቱ ከመጥራት ሃላፊነት በተጨማሪ የሙሐመድ አስተምህሮዎችንና የሃይማኖቱን መሠረታዊ መመሪያዎች የመፈፀም ግዳጅ አለበት፡፡ ይህ፣ ከሃይማኖቱ ውጪ ያሉ ሰዎችን ወደ እምነቱ የመጋበዝ ሥራ ዳዋ (dawah) በመባል ይታወቃል፡፡
         
ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ሙስሊሞች በዚህ የመነቃቃት ወኔ በመነዳት ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሃይማኖታቸውን ታላቅነት ለማሳየት በክርስትናና በአስተምህሮቱ ላይ በጭካኔ የተሞላ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ማንም ሊገነዘበው እንደሚችል እንደዚህ አይነቱ ከሃይማኖቱ ውጪ ያሉ ሰዎችን ወደ እምነቱ የመጥራት አካሄድ ሰውን በማክበርና በትህትና ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በሌላው ሰው የተቀደሰ እምነት እና ልማዶች ላይ የሚካሄድ እንዲህ አይነቱ በጭካኔ የተሞላ አቀራረብ ጥላቻና አለመረጋጋትን ከመፍጠር የዘለለ ምንም ፋይዳ ሊኖረውም አይችልም፡፡ አንዳንድ ስሜታዊ ክርስቲያኖችም የዚህ ችግር አካሎች እንደነበሩ መደበቅ አስፈላጊ መስሎ አይታየንም፡፡ የክርስቶስን ትምህርት በአግባቡ ያልተገነዘቡ እንደ እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች፣ የእስልምናን ነብይ ስም አንጓጠዋል፣ በእስልምና ባሕልና ልማዶች ላይም የስድብ ቃል ሰንዝረዋል፡፡ ይህ ተግባር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪክ ውስጥ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በሙሐመድ ዘመን እንኳን በእስልምና እምነት ላይ ያላግጡ የነበሩና ራሳቸውን ‘ክርስቲያን’ እያሉ የሚጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ቁርአን ይናገራል፡፡ በእነዚህ ላይ ቁርአን እንዲህ ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ያስተላልፋል፡-

Ø  እናንት ያመናችሁ ሆይ! [ሙስሊሞች ሆይ!] ይሁዶችና ክርስቲያኖችን ረዳቶች [ወዳጆች] አድርጋችሁ አትያዙ፣ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፣ ከእናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ በእነርሱ ነው፣ አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡ … እናንት ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከበፊታችሁ መጽሐፍን ከተሰጡት [ይሁዶችና ክርስቲያኖችን] እነዚያን ኃይማኖታችሁን ማላገጫና መጫወቻ አድርገው የያዙትን ከሃዲዎችንም ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፣ ምእመናንም እንደሆናችሁ አላህን ፍሩ፡፡
ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡51፣57

O ye who believe! Take not the Jews and the Christians for your friends and protectors … take not for friends and protectors those who take your religion for a mockery or sport.

በዚያ ዘመን የነበሩትናና እንዲህ አይነቶቹን አይሁድና ክርስቲያኖች ከሚያስጠነቅቀው ከፍ ብሎ ከተገለጸው ጥቅስ በተቃራኒው፣ ቁርአን ስለ ክርስቲያኖች የሚናገረው በርካታ አዎንታዊና ገንቢ ጥቅሶች አሉት፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የስም ክርስቲያኖችን ሳይሆን እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እስቲ ከዚህ በታች የተገለፁትን የቁርአን ጥቅሶች ለአብነት እንመልከት፡-

Ø  ይሁዶችንና እነዚያን ያጋሩትን ለነዚያ ለአመኑት [ሙስሊሞች] በጠላትነት ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የበረቱ ኾነው በእርግጥ ታገኛለህ፣ እነዚያንም እኛ ክርስቲያኖች ነን ያሉትን ለነዚያ ለአመኑት [ለሙስሊሞች] በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ሆነው ታገኛለህ፤ ይህ ከነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመሆናቸው ነው፡፡ [2]
 ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡82

… nearest among them in love to the believers (Muslims) wilt thou find those who say, “We are Christians” because amongst these are men devoted to learning and men who have renounced the world, and they are not arrogant.

Ø  ዒሳ [ኢየሱስ] ከእነርሱ ክህደት በተስማው ጊዜ፡- ወደ አላህ (ተጨምረው) ረዳቶቼ እነማን ናቸው? አለ፣ ሐዋሪያት፡- እኛ የአላህ ረዳቶች ነን፣ በአላህ አምነናል፣ እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መሆናችንን፣ መስክር አሉ፡፡ ጌታችን ሆይ! ባወረድኸው አመንን፣ መልዕክተኛውንም ተከተልን፣ ከመስካሪዎችም ጋር መዝግበን (አሉ)፡፡
 ሱረቱ አሊ-ዓምራን (3)፡52፣53

When Jesus found unbelief on their part, he said, “Who will be my helpers to (the work of) God?” Said the disciples: “We are God’s helpers; we believe in God, and do thou bear witness that we are Muslims (those who bow to God’s will). Our Lord! We believe in what Thou hast revealed, and we follow the Apostle (Jesus): then write us down among those who bear witness.”

Ø  እናንተ ያመናችሁ ሆይ [ሙስሊሞች] የመርየም [የማርያም] ልጅ ዒሳ [ኢየሱስ] ለሐዋሪያቶቹ ወደ አላህ ረዳቴ ማነው?እንዳለ ሐዋሪያቶቹም እኛ የአላህ ረዳቶች ነን እንዳሉት፣ የአላህ ረዳቶች ሁኑ፣ ከእሥራኤልም ልጆች አንደኛዋ ጭፍራ አመነች፣ ሌላይቱም ጭፍራ ካደች፣ እነዚያን ያመኑትንም በጠላታቸው ላይ አበረታናቸው፣ አሸናፊዎችም ሆኑ፡፡
 ሱረቱ ኣል-ሶፍ (61)፡14

Said the Disciples (of Jesus), “We are God’s helpers!” Then a portion of the Children of Israel believed (became followers of Jesus), and a portion disbelieved. But We gave power to those who believed against their enemies, and they became the ones that prevailed.

Ø  አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ ዒሳ [ኢየሱስ] ሆይ! እኔ ወሳጅህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፤ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ፣ አነዚያንም የተከተሉህን፣ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ፣ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤ በእርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ፡፡
 ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡55
Behold! God said: “O Jesus! I will take thee and raise thee to Myself and clear thee (of the falsehoods) of those who blaspheme. I will make those who follow thee superior to those who reject faith to the Day of Resurrection"

Ø  ከዚያም በዱካዎቻቸው ላይ መልዕክተኞቻችንን አስከታተልን የመርየምን [የማርያምን] ልጅ ዒሳንም [ኢየሱስንም] አስከተልን፤ ኢንጂልንም [ወንጌልንም] ሰጠነው፤ በነዚያም በተከተሉት (ሰዎች) ልቦች ውስጥ መለዘብንና እዝነትን፣ አዲስ የፈጠሩዎትንም ምንኩስና አደረግን
 ሱረቱ አል-ሐዲድ (57)፡27

We sent after them (the prophets) Jesus the son of Mary, and bestowed on him the Gospel; and We ordained in the hearts of those who followed him Compassion and Mercy.

ከሙስሊሞች ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ወቅት፣ ሆን ብለውም ሆነ ባለማወቅ ሃይማኖታቸውንና ነቢያቸውን ስለተሳደቡ ክርስቲያኖች ይቅርታ ለመጠየቅ ወደኋላ አትበል፡፡ የቁርአን አስተምህሮዎችን የማትቀበል ቢሆንም እንኳ፣ አንተ ሙስሞችን ከሚወዱና ቁርአን ከሚያወድሳቸው ከእውነተኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች መካከል እንደሆንክ ራስህን ልታስመሰክር ይገባል፡፡ ቃልህና ተግባርህ በአንዱ - በአብርሃም፣ በይስሃቅና በያዕቆብ አምላክ የምታምንና ለእርሱም ፈቃድ የምትገዛ መሆንህን ለሙስሊም ወዳጅህ ሊመሰክሩለት ይገባል፡፡ ለመማር የተሰጠህ፣ ከዓለማዊ እሥራቶች የተፈታህ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የምታገለግል፣ በጠላት ላይ የእግዚአብሔርን ኃይል የምትለማመድ፣ እስከ መጨረሻው የምትፀናና የምትበረታ በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ርህራሄና ምህረት ያለህ መሆንህን በፍቅር የምትገልጥለት ሁን፡፡ በእነዚህ ሁኔታ ራስህን የምትገልጥ ከሆንህ የእስልምና እምነት ተከታዮችን የልብ በር ለማግኘትና ለማገልገል ያለጥርጥር ተሳካልህ ማለት ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘን፣ ይህ መጽሐፍ የሙስሊሞችን አስተምህሮ በማጥቃት ወይም የጥቃት ምላሽ በመስጠት መንፈስ አለመቅረቡን በአፅንኦት ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደ ክርክር ማጣቀሻ ጽሑፍ ተደርጎ በሚነበብበት አቅጣጫም አልተጻፈም፡፡ አስተውል፣ እንደ እውነተኛ የጌታ ኢየሱስ ተከታይ ለሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማሳሰቢያ ልብህን ልትሰጥ ይገባል፡-

Ø  ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፣ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
 2ጢሞቴዎስ 2፡23-26
         
Ø  ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።
ቲቶ 3፡1-2

ይህ መጽሐፍ፣ በተለያየ መንገድ የቀረቡ የተለያዩ ጸሐፊዎች ጭምቅ አሳብና ከ 15 ዓመታት በላይ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ በመኖር ያካበትኩት የግል ልምዴ ውሁድ ውጤት ነው፡፡ በቀጣዮቹ ገጾች ውስጥ ያሉ ፍሬ አሳቦች በክርስቲያኑ ማህበረሰብ መካከል ጥርጥርና ግራ መጋባት ለመፍጠር፣ በክርክር አዋቂ ሙስሊም ሊቃናት ያለማቋረጥ በሚደረገው ዘመቻ ለሚደናገሩ አማኞች መረጃ በማቅረብ ረገድ የራሱ የሆነ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እምነታችን ነው፡፡

ክርስቲያኖች፣ ጥብቅና የሚቆሙለትን እውነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሌሎች ለመመስከር የሚያስችላቸው ብቸኛው መንገድ፣ የሚናገሩትን እውነት በሕይወት ኖሮ በማሳየት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል! በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መከባበርን ማስፈንና ወዳጅ መሆን ከማንኛውም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የሚጠበቅ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ የቃላት ጥቃትና መልሶ ማጥቃት መጨረሻው፣ ሽንፈት ብቻ ነው፡፡ የዚህም ነገር የሩቅ ጊዜ ውጤት፣ ቅሬታና ብስጭት ከመፍጠር የዘለለ አይሆንም፡፡ በትህትና እየኖሩ በየዕለቱ የሰውን ጠንካራ ልብ ሊያሸንፍ የሚችለውን የክርስቶስን ፍቅር በተግባር እየገለጡ ከመኖር በቀር፣ ሙስሊም ወዳጆችን ለማፍራት ምን የተሻለ መንገድ ሊኖረን ይችል ብለው ያስባሉ?

በዚህ መጽሐፍ ስር የቀረቡ መረጃዎች፣ በወዳጅነት እና በጋር መከባበር ላይ በተመሠረተ አቀራረብ ጥቅም ላይ እስከዋሉ ድረስ፣ በቅንነት እውነትን ለማወቅ ለሚሹ ሙስሊም ጠያቂዎች መልስ ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ እምነታችን ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ በግልፅ፣ እምነትን የመነጋገር ልምድ ሙስሊም ወዳጅዎ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቅ እውነቶች ለመመርመር እንዲነሳሳ ያግዘዋል፡፡ የዚህ ፍጻሜው ደግሞ በመሲሁ ኢየሱስ የሚገኘውን ድኅነት/መዳን የማወቅ እድል መፍጠር ይሆናል፡፡

እውነተኛዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በታሪክ በመሳሪያም ሆነ በቃል ጦርነት ውስጥ ራሳቸውን አላሳተፉም፡፡ በእዚህ ፈንታ ዓለማዊ ግቦቻቸውን ወደጎን በማድረግ ወንጌልን ለሰው ልጆች ሁሉ ለማድረስ ራሳቸውን ሰጡ እንጂ፡፡ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ታማኝ በመሆን የክርስቶስን ፍቅር መግለጥ፣ በስሙም የሚገኘውን ድኅነት/መዳን እና የኃጢአት ስርየት መስበክ ዋነኛ ተልዕኮአቸው ነበር፡፡ ማንንም አልኮነኑም፣ አይኮንኑምም፡፡ ከእዚህ ይልቅ እንደ ክርስቶስ አምባሳደሮች፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲተራረቁ የማስታረቅን አገልግሎትን ሊያውጁ ተገባቸው! ይህንን ክቡር ተጋድሎ እግዚአብሔር ይባርክ፡፡)
__________________________
[1] ታልሙድ፡- የአይሁድን የፍትሐ ብሔርና የሃይማኖት ሕግ የያዘ የጽሑፍ ስብስብ ነው::
[2] ይህ ስለ ኢትዮጵያ ነጋሢ ልዑካን የተነገረ ነው ይባላል (ከቅዱስ ቁርአን የግርጌ ማስታወሻ የተወሰደ

PageRank