Monday, March 5, 2012

18. ‹የበርናባስ ወንጌል› እውነተኛ ወንጌል ነው

18. ‹የበርናባስ ወንጌል› እውነተኛ ወንጌል ነው

አዲስ ኪዳን ዋናው የወንጌል ቅጂ አይደለም የሚሉ አንዳንድ ሙስሊሞች ‹ትክክለኛ› ነው የሚሉትን ለማግኘት ውጤት አልባ ልፋት ለፍተዋል፡፡ በመጨረሻ ላይ እነዚህ ፈላጊዎች ሊያደርጉት የቻሉት ‹ትልቁ ነገር› ቢኖር ‹የበርናባስ ወንጌል› የሚባል መጽሐፍን ለዚህ ጥያቄያቸው እንደ መልስ ማቅረብ መቻላቸው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ተጻፈ የሚባለው በሐዋሪያው ጳውሎስ የመጀመሪያው የሚሽነሪ ጉዞ ወቅት አብሮት በነበረው አማኝ ‹‹በርናባስ ነው›› (የሐዋሪያት ሥራ 13፡1-4)፡፡ አንድ ዘመናዊና ጥልቅ ጥናት ስለዚህ ‹የበርናባስ ወንጌል› ስለ ተሰኘው መጽሐፍ የሚከተለውን ያስነብበናል፡-

በርካታ ቀደምት ጸሐፍት በሥራዎቻቸው ‹የበርናባስ ወንጌል› የሚል ርዕስ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ርዕስ በገላሲየስ አዋጅ (500ዓ.ዓ.) ‹‹Decree of Galasius›› ውስጥም ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን ርዕሱን ከመጥቀስ ውጪ ስለ ሥራው ይዘትም ሆነ ገጸ-ባሕሪያት በነዚህ ማጣቀሻ መጻሕፍ ውስጥ ምንም የተባለ ነገር አይገኝም፡፡ ይሁንና፣ ‹የበርናባስ ወንጌል› የሚል ርዕስን በላዩ የያዘ በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈ ረቂቅ በአሁኑ ሰአት ይገኛል፡፡ ረቂቁ ጠንካራ የኖስቲሲዝም/Gnosticicm [16] አሳብን የሚያንጸባርቅና ከሙስሊም አቋም አንጻር የተጻፈ ነው፡፡  መጽሐፉ በ 1907 በሎንስዳል እና በላውራ (ኤም ሮበርትስ) ራግ አርትኦት ተደርጎበታል፡፡ መጽሐፉ፣ እንደ ብዙዎቹ የመካከለኛ ዘመን የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች/ patrisitic እና መቃቢያን/apocrypha፣ እጅጉን አሳባዊ ነው፡፡ ግልጽና ጠንካራ ሥነ-ምግባራዊ ይዘት ቢኖረውም ሥራው በታሪካዊ እዉነታዎች ላይ ያልተመሰረተና ልብ-ወለዳዊ ነው፡፡
 ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና
 የ1976 ህትመት፣ ገጽ 247

በመጽሐፉ አወዛጋቢ ባሕሪ ምክንያት፣ ለ ‹የበርናባስ ወንጌል› መጽሐፍ ትኩረት የሚሰጡት በጣም ጥቂት ሙስሊሞች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስትናን ስሜታዊ በሆነና ማስረጃ በጎደለው መንገድ ለማጥቃት በብርቱ የሚመኙቱ ናቸው፡፡ በእስልምና እውቀት የገፉና የፍልስጤምን መልክአ ምድርና ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሁሉ ለዚህ መጽሐፍ መለኮታዊ መሰረት መስጠት በእስልምና ላይ ግልጽና አሳፋሪ ድርጊት መፈጸም እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ‹የበርናባስ ወንጌል› መጽሐፍ፣ ቁርአንንና በኢየሱስ ዘመን የነበረውን የፍልስጤም ታሪካዊ ዳራ በጉልህ ይጻረራል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ከዚህ በታች በየፈረጁ ተዳሰዋል፡-

የመሲሁ ማንነት
ከበርናባስ መጽሐፍ (ህትመት 1907) ዋነኛ አላማዎች መካከል አንዱ የመሲህነትን መዕረግ (ስያሜ) ከኢየሱስ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ ማሻገር ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሙከራ በውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ማስረጃዎች አንጻር የሚያመጣው ግጭት ግልጽ ነው፡፡
         
የሚከተሉት መረጃዎች የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹መሲህ›› የሚለውን ስያሜ ከኢየሱስ ላይ ለማንሳት ላደረገው ጥረት አስረጂዎች ናቸው፡፡

ገጽ 122፣ ምዕራፍ 96፡ ኢየሱስ እኔ መሲህ አይደለሁም አለ
ገጽ 123፣ ምዕራፍ 97፡ ሙሐመድ መሲሁ ነው
ገጽ 182፣ ምዕራፍ 142፡ መሲሁ ከዳዊት ወይም ከይስሃቅ ዘር ግንድ አይደለም

ከላይ ከተገለጸው መረጃ በተቃራኒው ቁርአን አል-መሲህ (መሲሁ) የሚለውን ማዕረግ ከማሪያም ልጅ ከኢየሱስ በቀር ለማንም አለመስጡን በግልፅ ያስነብበናል፡፡ መሲህ የሚለው ልዩ ስያሜ በቁርአን ውስጥ ነቢዩ ሙሐመድን ጨምሮ ለማናቸውም ሌሎች ነቢያት አልተሰጠም፡፡ የሚከተሉትን የቁርአን ጥቅሶች እንመልከት፡-

Ø  እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ፤ የመርየም [የማሪያም] ልጅ አልመሲሕ [መሲህ] ዒሳ [ኢየሱስ] የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት (የኹን) ቃሉም ከርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነዉ፤ …
ሱረቱ አል-ኒሳእ (4)፡171

Christ Jesus (Al-Masih Isa) the son of Mary was (no more than) an apostle of God, and His Word, which He bestowed on Mary, and a Spirit proceeding from Him.
Ø  መላእክት ያሉትን (አስታውስ)፡- መርየም [ማሪያም] ሆይ! አላህ ከእርሱ በሆነው ቃል ስሙ አልመሲህ [መሲህ] ዒሳ [ኢየሱስ] የመሪየም ልጅ በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ ከባለሟሎችም በሆነ (ልጅ) ያበስርሻል፡፡
ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡45

Behold! The angels said: “O Mary, God giveth thee glad tidings of a Word from Him; his name will be Christ Jesus (Al-Masih Isa), the son of Mary, held in honor in this world and the hereafter.”

ሙስሊሞች ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ኢየሱስ ከአብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ ዘር፣ ከነቢዩ ዳዊት ሥር የተገኘ አይሁዳዊ መሲህ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹የበርናባስ ወንጌል› ከዚህ እውነት በተቃራኒው መሲሁ ከዳዊት ወይም ከይስሃቅ ዘር ግንድ አልተገኘም ማለቱ በግልጽ ከሙስሊም እምነት ጋር የሚቃረን መሆኑን ያሳየናል፡፡

የበርናባስ መጽሐፍ ደራሲ በመጽሐፉ ዳር እስከ ዳር ለኢየሱስ፣ ክርስቶስ የሚል ስያሜ ሰጥቶ ሲያበቃ መልሶ ኢየሱስ መሲህ አይደለም ብሎ ይከራከራል! ክርስቶስ ማለት መሲህ ማለት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የተዛቡ ጥቅሶችና የባህሎች
ገጽ 5፣ ምዕራፍ 3፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ ማርያም ያለምንም ስቃይ ኢየሱስን እንደ ወለደች ተጠቅሷል፡፡ ቁርአን ግን በተቃራኒው የሚከተለውን ያስነብበናል፡-

Ø  ወዲየውኑም አረገዘችው፤ በርሱም (በሆድዋ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች፤ ምጡም ወደ ዘንባባዬቱ ግንድ አስጠጋት፣ ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ፤ ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ አለች፡፡
ሱረቱ መሪየም (19)፡22-23

So she conceived him (Jesus), and she retired with him to a remote place. And the pains of childbirth drove her to the trunk of a palm-tree: She cried (in her anguish): “Ah! Would that I had died before this!”

ገጽ 26፣ ምዕራፍ 23፡ እዚህ ክፍል ላይ ደግሞ ግዝረት በአዳም እንደ ተጀመረ ይናገራል፡፡ ነገር ግን የእስማኤላውያን ባሕልም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ስርአት በአብርሃም እና እስማኤል ማህበረሰብ ወቅት እንደ ተጀመረ ይናገራሉ፡፡

ገጽ 46፣ ምዕራፍ 35፡ ይህ ምዕራፍ፣ የሰው እንብርት ከሰይጣን አክታ መሰራቱን ያስነብበናል፡፡ በገጽ 50፣ ምዕራፍ 39 ላይ ደግሞ ‹‹የበርናባስ ወንጌል›› ደራሲ ውሻ ከሰይጣን አክታ ነው የተፈጠረው ይለናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቁርአን ሰይጣን በሰው ልጅ አፈጣጠር ውስጥ (የሰውን እንብርት ጨምሮ) ድርሻ እንደ ነበረው የሚጠቁሙን ነገር የላቸውም፡፡ በተጨማሪም፣ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔር በፍጥረት ሥራው ውስጥ የሰይጣንን እርዳታ እንደማይሻ የበርካታ ሙስሊሞች እምነት እንደሆነ እርግጠኞች ነን!

ገጽ 51፣ ምዕራፍ 39፡ ይህ ክፍል ደግሞ አዳምና ሔዋን የፖም ፍሬንና በቆሎን እንዳይበሉ እንደተከለከሉ ያስነብበናል፡፡ ነገር ግን ቁርአኑ የሚከተለውን ይላል፡-

Ø  አዳም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ በገነት ተቀመጥ፤ ከእርሷም በፈለጋችሁት ስፍራ በሰፊው ተመገቡ፤ ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤ ከበደለኞች ትሆናላችሁና አልንም፡፡
ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡35
O Adam! Dwell thou and thy wife in the Garden; and eat of the bountiful things therein as (where and when) ye will: but approach not this tree, or ye run into harm and transgression.

‹‹ፖም›› እንዳይበላ ከታዘዙት የዛፍ ፍሬዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይችል ይሆናል፣ የእህል ዘር የሆነው ‹በቆሎ› ዛፍ ላይ አለመብቀሉ ግን እንግዳ ነገር ሊሆን አይችልም!

ገጽ 57፣ ምዕራፍ 44፡ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ ለይስሃቅ ዘር የተገባው የተስፋ ቃል ወይም ቃል ኪዳን ተሰርዟል የሚል እናነባለን፡፡ መጽሐፉ ይህን ቢልም ቁርአን እግዚአብሔር ቃል ኪዳንን ከእስማኤልና ከዘሩ ጋር ስለመገባቱ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ እንዲህ አይነቱ የተስፋ ቃል ወይም ቃል ኪዳን ከይስሃቅ ማለትም ከእሥራኤል (ከያዕቆብ) እና ዘሩ ጋር በተያያዘ ግን በቁርአን ውስጥ ተጠቅሶ እናነባለን፡፡ የሚከተለውን የቁርአን ጥቅስ እናንብ፡-

Ø  የእሥራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በእናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬን አስታውሱ፤ በቃል ኪዳኔም ሙሉ፤ በቃል ኪዳናችሁ እሞላለሁና፤ እኔንም ብቻ ፍሩ፡፡
ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡40

O Children of Israel! Call to mind the (special) favor which I bestowed upon you, and fulfill your covenant with Me as I fulfill My Covenant with you, and fear none but Me.

ገጽ 132፣ ምዕራፍ 105፡ ይህ ክፍል ስለ ‹‹ዘጠኝ›› ሰማያት ሲጠቅስ ቁርአን ግን ስለ ሰባት ሰማያት ብቻ ነው የሚያወራው፡፡

Ø  እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለናንተ የፈጠረ ነው፤ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፤ እርሱም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው፡፡
ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡29

Moreover His design comprehended the heavens, for He gave order and perfection to the seven firmaments;…

ገጽ 134፣ ምዕራፍ 106፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጀሀነም /ገሃነም (ሲኦል)/ ሊቋቋሙት በማይችሉት የበረዶ ግግር ስፍራ ተመስሏል፡፡ በርካታዎቹ የቁርአን ጥቅሶች ግን ይህን ስፍራ በሚቃጠል ነበልባልና በተንቀለቀለ (በፈላ) ውሃ ይመስሉታል፡፡

ገጽ 141፣ ምዕራፍ 112፡ ይህ ክፍል ደግሞ ኢየሱስ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ወደ ሰማይ እንደማያርግ መናገሩን ያስነብበናል፡፡ የሚከተለው የቁርአን ማስረጃ ግን በተቃራኒው እንዲህ ይላል፡

Ø  አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ ዒሳ [ኢየሱስ] ሆይ! እኔ ወዳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፤ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ፤ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከእነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነዉ፤ በርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ፡፡
ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡55

Behold! God said: “O Jesus! I will take thee and raise thee to Myself….”

Ø  ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ሱረቱ አል-ኒሳእ (4)፡158
         
Nay, God raised him up unto Himself; and God is exalted in power, Wise.

ገጽ 156፣ ምዕራፍ 124፡ እዚህ ክፍል ላይ፣ ዛቡር [መዝሙረ ዳዊት] የተሰጠበት ምክንያት ቶራ [የሙሴ መጻሕፍት] ስለተበረዘ መሆኑና ኤንጅል [አዲስ ኪዳን] የተሰጠው ደግሞ የዛቡር መጽሐፍ በመበረዙ ምክንያት እንደሆነ ተገልጸ_ል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ የምክንያት ዝርዝር በቁርአኑ ውስጥ አልተገለጸም፡፡ በታቃራኒው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍት ለሰው ዘር ምሪቶችና ብርሃኖች እንደሆኑ ይመሰክርላቸዋል እንጂ፡፡ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት ተበርዘው ቢሆን ኖሮ ቁርአን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ባላለ ነበር፡-

Ø  እነሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸው ወደነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሰሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ስር በተመገቡ ነበር፤ …[በሙሴ መጻሕፍት፣ በወንጌል እና ከጌታቸው ወደ እነሱ በወረዱ መገለጦች ጸንተው ቢኖሩ ኖሮ ደስታን በሁሉ የሕይወት አቅጣጫ በተለማመዱ ነበር፡፡]
ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡66

If only they had stood fast by the Law, the Gospel, and all the revelation that was sent to them from their Lord, they would have enjoyed happiness from every side.

Ø  እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው፣ በዚያም በመልክተኛው፣ ላይ ባወረደዉ መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ [ከቁርአን በፊት በወረዱት ቅዱሳት መጻሕፍት ማለትም በሙሴ መጻሕፍት፣ በነቢያት መጻሕፍት እና በወንጌል እመኑ]፤ በአላህና በመላእክቱም በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም በመጨረሻዉም ቀን የካደ ሰው (ከዉነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ፡፡
ሱረቱ አል-ኒሳእ (4)፡136

O ye who believe! Believe in God and His apostle, and the scripture which He hath sent to His apostle and the scripture which He sent to them before him. Any who denieth God, His angels, His Books, His Apostles, and the Day of Judgment hath gone far, far astray

ገጽ 273፣ምዕራፍ 221፡ በዚህ ክፍል ላይ ደግሞ ኢየሱስ ‹‹አልሞትኩም፡፡›› ብሎ ሲናገር ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳ በርካታ ሙስሊሞች የኢየሱስን ሞት ቢክዱም ቁርአን ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ምንም ግልጽ ማስረጃ አይሰጥም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን፣ ቁርአኑ ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ከማረጉ በፊት እንደ ሞተ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጣል፡፡ የሚከተለውን የቁርአን ማስረጃ እንመልከት፡-

Ø  አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ ዒሳ [ኢያሱስ] ሆይ! እኔ ወዳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፤ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ፤ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከለዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነዉ፤ በርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ፡፡
ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡55

Behold! God said, “O Jesus, I will take thee and raise thee to Myself….”

‹‹እኔ ወሳጅህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ›› የሚለው አባባል አረብኛ አገላለጽ ታዋፊቅ/tawaffik ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹እንድትሞት አደርግሃልሁ፡፡›› ማለት ነው፡፡ ይህ አባባል በሱረቱ-አል መኢዳህ (5)፡117 አንቀጽ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በዚህም ስፍራ ላይ ያለው የቃል በቃል አረብኛ አገላለጽ ትርጉም፣ ‹‹እንድሞት ባደረግኸኝ ጊዜ›› ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ከማረጉ አስቀድሞ ስለ መሞቱ ሌላም አስረጅ ጥቅስ አለ፡፡ በዚህ ክፍል ላይ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተጠቅሷል፡-

Ø  ሰላምም በኔ ላይ ነው፣ በተወለድሁ ቀን በምሞትበትም ቀን ሕያው ሆኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፤
ሱረቱ መሪየም (19)፡33

So peace is on me the day I was born, the day that I die, and the day that I shall be raised up to life (again)!
ቅዱስ ቁርአን፡- ትርጉምና ማብራሪያ፣ (በኤ. ዩሱፍ አሊ)፣ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 2485 እንዲህ ይላል፣ ‹‹…እርሱ (ኢየሱስ) አልሞተም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ስለዚህ ጥቅስ አጥብቀው ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡›› ስለዚህ ጉዳይ አንስተው በርካታ ሙስሊሞች ምላሽ ለመስጠት ሲጥሩ፣ ኢየሱስ የሚሞተው ዳግመኛ ወደ ምድር ሲመለስ ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ይበሉ እንጂ ይህ አስተምህሮ በቁርአን ውስጥ የለም!

እዚህ ላይ ሌላ ጠቃሚ ነጥብ እንመልከት፡፡ ጉዳዩ መጥምቁ ዮሐንስን ይመለከታል፡፡ ሙስሊሞች የሕያ እያሉ የሚጠሩት መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ ‹የበርናባስ ወንጌል› በሚሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ፈጽሞ ያልተጠቀሰ ሲሆን በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ታላቅ ስፍራ ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡ የሕያ (መጥምቁ ዮሐንስ) ከኢየሱስ ፊት በመሄድ ስለ ኢየሱስ መምጣት ይመሰክር የነበረ አገልጋይ ነበር፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ተቀዳሚ ተልኮ ደግሞ መሲሁ ኢየሱስ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀባ መሆኑን ማረጋገጥ ነበር፡፡ የበርናባስ ደራሲ ለምን መጥምቁ ዮሐንስን ከመጽሐፉ ፈፅሞ መደምሰስ እንደፈለገ አሁን ፍንትው ብሎ የሚታይ ይመስለናል፡፡ ይህ ደራሲ ሙሐመድን መሲህ ለማድረግ የመጥምቁ ዮሐንስን አገልግሎት በማስወገድ፣ ኢየሱስ የመጥምቁ ዮሐንስን ቦታ እንዲተካና ‹‹የመሲሁ›› ሙሐመድ ምስክር ማድረግ ነበረበት፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በኃላ ይህ መጽሐፍ ከቁርአን ትምህርቶች ጋር የሚጣረስ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ብለን እናምናለን!

የተዛቡ ምልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች
ምዕራፍ 20፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ ‹‹…ኢየሱስ በጀልባ በመሳፈር የእርሱ ከተማ ወደሆነችው ናዝሬት ተጓዘ›› የሚል ዐረፍተ ነገር እናነባለን፡፡ እውነታው ግን ናዝሬት በደረቅ መሬት ላይ የተከተመች ከተማ መሆኗ እንጂ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ እንደሚነግረን የወደብ ከተማ መሆኗ አይደለም፡፡

ምዕራፍ 21፡ እዚህ ላይ ደግሞ ‹‹ወደ ቅፍርናሆም በእግሩ ተጓዘ፡፡›› የሚል ዐረፍተ ነገር እናነባለን፡፡ ነገር ግን ቅፍርናሆም በገሊላ ባሕር የምትገኝ የወደብ ከተማ መሆንዋን ልብ ይሏል፡፡

ምዕራፍ 92፡ በዚህ ገጽና ምዕራፍ ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሲና ተራራ ከወጣ በኃላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ቀረበ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ነገር ግን የሲና ተራራ በስተ ግብጽ በኩል ባለው የእሥራኤል ክፍል የሚገኝ ሲሆን፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ደግሞ በስተ ዮርዳኖስ በኩል ባለው የእሥራኤል ክፍል የሚገኝ ወንዝ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ቦታዎች በጣም የሚራራቁ ቦታዎች ናቸው!

ምዕራፍ 169፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ ‹‹ሁሉ ነገር ፍሬ አዝሎ በሚታይበት የበጋ ወራት ይህ ስፍራ እንዴት ውብ ነው፡፡›› የሚል አገላለጽ ሰፍሮ እናነባለን፡፡ እርግጥ ነው፣ ይህ አገላለጽ እንደ አውሮፓ ባሉ አካባቢዎች ላይ ሲነበብ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ መሬቱ ክው በሚልበትና ከሚባላው ፀሀይ የተነሳ ምድር ፍሬዋን በምትከለክልበት በፍልስጤም የበጋ ወራት አውድ ሲነበብ ግን አባባሉ ተቃራኒ ትርጉም ከመስጠት ውጪ ሊላ አማራጭ ሊኖረው አይችልም፡፡

ምዕራፍ 3፡ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ፣ ‹‹አናኒያና ሰጲራ ካህናት በሆኑበት ዘመንና ፒላጦስ ደግሞ ገዢ በሆነበት ዘመን ኢየሱስ ተወለደ›› ሲል ያስነብበናል፡፡ ከታሪክ የምንረዳው ደግሞ፣ ፒላጦስ ከ26-27 ዓ.ም. በፊት ገዢ እንዳልነበረ ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ ‹‹የበርናባስ መጽሐፍ›› ፒላጦስን ባልኖረበት ዘመን ገዢ እንዳደረገው እንመለከታለን፡፡

ምዕራፍ 12፡ በዚህ ገጽና ምዕራፍ ላይ ደግሞ ‹‹ወደ ቤቱም ሰገነት ላይ ወጣ›› የሚል ዐረፍተ ነገር እናነባለን፡፡ ይሁንና ይህ አባባል፣ አውሮፓ ውስጥ ንግግሮች በረጃጅም ሰገነቶች ላይ የሚሰጡበትን የ15ኛውንና 16ኛውን መካከለኛው ክፍለ ዘመን የሚገልጥ እንጂ በምኩራቦቻቸው ውስጥ ስብከቶች የሚሰጡባቸውን የአይሁድና ፍልስጤማውያንን ታሪክ ፈጽሞ አይወክልም፡፡

ምዕራፍ 18፡ በዚህ ክፍል ላይ ደግሞ፣ 10000 የሚሆኑ ነቢያት ኤልዛቤል በተባለች ሴት መታረዳቸው ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ይህ ጉዳይ በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በታሪክ ድርሳናት ላይ ፈጽሞ ተጠቅሶ አናነብም፡፡

ምዕራፍ 32፡ በዚህ ክፍል ላይ መጽሐፉ የበአል ጣኦት አምልኮ በዓለም ገጽ ሁሉ ተንሰራፍቶ እንደ ነበር ያስነብበናል፡፡ ሆኖም ይህንን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት የአርኪዮሎጂ [18] ጥናት ማስረጃ አልተገኘም፡፡

ገጽ 82፣ ምዕራፍ 65፡ በዚህ ገጽና ምዕራፍ ላይ ደግሞ የመዋኛ ገንዳን ለመጥቀስ ፕሮባቲካ (probatica) የተሰኘ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ እናገኛለን፡፡ ሆኖም ይህ ቃል የግሪክ ሆኖ ከኢየሩሳሌም ደጆች መካከል አንዱ ለሆነውን ‹‹የበጎች በር›› ስያሜ የዋለ ነው፡፡

ምዕራፍ 91፡ በዚህ ክፍል ላይ 600000 የሚደርሱ የሮም ወታደሮች ሚዝፔህ (Mizpeh) በተሰኘች ትንሽ መንደር ውስጥ ተከማችተው እንደ ነበረ ተገልጸ_ል፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ከፍተኛ ግነት ከመሆኑ በተጨማሪ በሮም የታሪክ መዛግብት ላይ የማይገኝ ታሪክም ጭምር ነው፡፡

ምዕራፍ 103፡ ‹‹መርከበኛ›› እና ‹‹መርከብ›› የሚሉት ቃላት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህ ቃላት ኢየሱስ አገልግሎቱን ይፈጽምበት በነበረበት ዘመን በፍልስጤም አካባቢ የተለመዱ ቃላት አልነበሩም፡፡ እነዚህ ቃላት ይበልጥ የመካከለኛውን ዘመን የስፔን እና የጣልያን አካባቢዎች የሚገልጹ ናቸው፡፡

ምዕራፍ 145፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ በነቢዩ ኤልያስ ዘመን 17000 የሚሆኑ ፈሪሳውያን መኖራቸው ተገልጸ_ል፡፡ እውነታው ግን ፈሪሳውያን ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 200 ዓመት ዓለም፣ የአይሁድ መቃቢያን ዘመን ድረስ ያልነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ኤሊያስ ደግሞ ከዚህ ዘመን 700 አመት በፊት፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ900 ዓ.ዓ. የኖረ ነቢይ ነበር፡፡

ምዕራፍ 152፡ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ ‹‹ወይን ከመሞላታቸው በፊት ለመታጠብ እንደተደረደሩ፣ ከእንጨት እንደተሰሩ የአልኮል መጠጥ በርሜሎች፣ ወታደሮች በዝግታ ሲያልፉ…›› የሚል አገላለጽ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ሆኖም ግን በኢየሱስ የአገልግሎት ዘመን ከእንጨት የተሰሩ በርሜሎች የተለመዱ አልነበሩም፡፡ የዛን ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ በእነዚህ ስፍራዎች የወይን ማስቀመጫዎች ከእንስሳ ቆዳ እንጂ ከእንጨት በርሜሎች አይሰሩም፡፡ ከእንጨት የተሰሩ የወይን በርሜሎች፣ በወቅቱ ወደ ሌላ የዓለም ክፍል ሳይቀር ይላኩ የነበረበትን የመካከለኛ ዘመን አውሮፓ ታሪክን የሚገልጽ ነው፡፡

ምዕራፍ 214፡ በዚህ ገጽና ምዕራፍ ላይ ደግሞ ‹‹30 የወርቅ ቁራጮች›› የሚል አገላለጽ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ዘመን የፍልስጤም ገንዘብ የብር ቁራጮች ነበሩ፡፡

ማጠቃለያ፡- ከተሰጡት በርካታ ማስረጃዎች በመነሳት ሙስሊሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች ይህ ‹የበርናባስ ወንጌል› የተሰኘው መጽሐፍ መለኮታዊ መነሻ እንደሌለው ሊያውቁ ይገባል፡፡ ሁሉም ማስረጃዎች የሚጠቁሙት ይህ መጽሐፍ በአውሮፓ ውስጥ ምናልባትም በመካከለኛው ዘመን ወቅት ክርስትናን ለማጥቃት ይውል ዘንድ በአንድ ግለሰብ የተቀነባበረ የፈጠራ ሥራ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንድ ተመራማሪዎች ‹የበርናባስ ወንጌል› መጽሐፍ እስልምና በክርስቲያኖች አማካኝነት ከስፔን በመወገዱ ያዘነ፣ በዚህም ምክንያት ሙሐመድን ከኢየሱስ በላይ ለመሳል በሞከረ የስፔን ወይም የጣልያን ስረ መሠረት ባለው ግለሰብ የተጻፈ መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ፡፡ ይህ ሊታመን የማይችል የፈጠራ ሥራ እውነትን በሚሹ ሰዎች በማስረጃ በተደገፈ መልኩ እየተጋለጠ ነው፣ እውነት ሁል ጊዜ ታሸንፋለችና!

No comments:

Post a Comment